ቃጥባሬ   መስጅድ

የቃጥባሬ መስጂድ በጉራጌ ዞን በቀቤና ወረዳ ከዞኑና ከቀቤና ወረዳ ርእሰ ከተማ ወልቂጤ በስተምስራቅ አቅጣጫ 10 . ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ወልቂጤን ማዕከል አድርጎ ለተንቀሳቀሰ ተጓዥ መስጂዱን ለማግኘት ሁለት አማራጭ የመኪና መንገዶች ይኖሩታል፡፡ ይኸውም አንደኛው መንገድ በጣም ቅርብና ምቹ ሲሆን የወልቂጤ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ የሚወስደውን መንገድ ተከትሎ ኮሌጁን ጥቂት አለፍ ብሎ ጥርጊያ መንገድ ላይ 10 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ያገኙታል፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ከወልቂጤ ወደ ወሸርቤ ከተማ የሚወስደውን የጠጠር መንገድ 15 . ያህል ከተጓዙ በኋላ ስንኳ ቀበሌ ጤና ጣቢያ ሲደርሱ በስተቀኝ በኩል በመታጠፍ ወደ አምበልታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚወስደው ጥርጊያ መንገድ በግምት 2 . ከተጓዙ ወደ መስጂዱ ቅጥር ግቢ የሚያደርሰው ነው፡፡

የቃጥባሬ መስጅድ በዞኑ ውስጥ ከሚገኙ ቀደምት መስጅዶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ መስጅዱ 1870 በሼህ ኢሳ ሃምዛ የተመሰረተ ሲሆን ሼህ ኢሳ ለእስልምና ኃይማኖት መስፋፋት በነበራቸው ፅኑ ፍላጎትና ጉጉት የእምነቱን ትምህርት ለመማር ሰሜን ሸዋ (ይፋት) እና በወሎ ክፍለ ሀገር (ዳና) በመዘዋወር ብዙ ዓመታት የሃይማኖት ትምህርት ሲከታተሉ ቆይተው ከተመረቁ በኋላ ለኃይማኖቱ መስፋፋት እና ለቁርዓን ትምህርት ምቹ የሆነው ቃጥባሬን በመምረጥና የአካባቢውን ኅብረተሰብ በማስተባበር ይህን መስጅድ መመስረት ችለዋል፡፡

                       

ሼህ ኢሳ ሃምዛ 1883 እስከ 1928 ለቤተ መንግስት እጅግ ቀራቢ እንደነበሩ እና ለቀቤናና ለጉራጌ ህብረተሰብ ብዙ ፈርቀዳጅ የሆኑ ስራዎች እንደሰሩ ታሪክ ይመሰክርላቸዋል፡፡ እኚህ ሼህ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ምንም መስጂድ ባልነበረበት የአፄ ምኒሊክ ዘመን በወቅቱ የጦር ሚኒስቴር ከነበሩት ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ በማስፈቀድና የአ/ ሙስሊም ነዋሪ በማስተባበር በአዲስ አበባ የመጀመሪያ የሆነው የበኒ መስጂድ ከመስራታቸውም በላይ ለቡታጅራው ታሪካዊ መስጂድ መሰረት መጣል የቻሉ ታሪካዊ ሰው ናቸው፡፡

ከሼህ ኢሳ ሃምዛ አብራክ የተገኙት ሐጅ ሱልጣን (ሻለቃ ሱልጣን) የአባታቸውን ፈለግ በመከተል የኃይማኖቱን ስርዓት እጅግ በማስፋፋት የቡታጅራ ትልቁና ታሪካዊው መስጂድ አሁን ባለው መልኩ ከማስገንባት በተጨማሪ በተለያዩ የልማት ሥራዎችም በኩል የነበራቸው ሚና በቀቤናና በጉራጌ ታሪክ ውስጥ በልማት ባለቤትነት ከሚጠቀሱት ከሃጅ ፈቱዲነና ጄነራል /ስላሴ በረካ ተርታ የሚሰለፉ የልማት ሰው ነበሩ፡፡ ባሁኑ ወቅት የመስጂዱን ኃላፊነት ተረክበው እያስተዳደሩት ያሉት የሐጅ ሱልጣን ልጅ ሐጅ በድሩዘማንም ቢሆኑ መስጂዱን ታሪካዊነቱን እንደያዘ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማዛመድ የኃይማኖት ተቋም ብቻ ሳይሆን የልማት ተቋምም እያደረጉት ይገኛሉ፡፡

የቃጥባሬ መስጂድ ከሌሎች መስጂዶች ሁሉ ለየት የሚያደርገውና ልዩ መገለጫው የሆነው በመስጂዱ አከባቢ የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች በአረንጓዴ ብጫና ቀይ ቀለማት ያጌጠ የዕደ ጥበብ ውጤት ኮፍያ መልበሳቸው ሲሆን የኮፍያው ዲዛይንና የዲዛይኑ ቀለማት ሁለቱም የየራሳቸው የሆነ መልዕክት አላቸው፡፡ ይኸውም ሶስቱ ቀለማት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በመወከል አገራዊ ስሜት እንዳላቸው የሚያመላክት ሲሆን በአምስት አቅጣጫ የተቀመጡት ዲዛይኖች ደግሞ ከእስልምና እምነት አንፃር የፈጣሪን አምስቱ ዋነኛዎቹ ስሞች እንዲገልጹ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው፡፡

በዚህመስጅድ ውስጥ የተለያዩ ቅርሶች ማለትም ከጅማ አባ ጅፋር የተሰጠ ጥንታዊ ቁርአን፤ልዩ ልዩ ታሪካዊ ደብዳቤዎች፤በብራና ተፃፉ ቁርአኖችና ኪታቦች፤ከጣሊያኖች ተበረከተ ፋኖስ፤የሼሁ ማረፊያ አልጋ፤ለጥበቃ የሚያገለግሉ የተለያዩ የጥበቃ መሳሪያዎች(ጦሮች፤ጋሻዎችና ጎራዴዎች)፤ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች(ከድንጋይና ከእንቸት የተገነባ ባለ አንድ ፎቅ)፤የመቃብር ቤቶች ሀገር በቀል የሆኔ በርካታ ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ይገኛሉ፡፡

የየቃጥባሬ መስጅድ ቅጥር ግቢ በተፈጥሮ ደን፤በተለያዩ ፍራፍሬወችና አትክልቶች ተውቦ መንፈስን በማደስ ለጎብኚዎች ምቹና ማራኪ ከመሆኑም ባሻገር ቁጥራቸው በዛ ያሉ ኃይማኖታዊ ትምህርት መማርያና የእንግዳ ማረፊያ በሆኑ አነስተኛ መስጅዶችና ኸላዋዎች የተሞላ ነው፡፡

የመስጅዱ ተፈጥሮአዊ የግቢ ውበት እጅግ ማራኪ ሲሆን 100 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፈ እና በግቢው ሰፊ የእርሻ ልማት ስራዎች የሚከናወኑበት ነው፡፡ ግቢው በጣም ውብና ማራኪ በተለይም ለመስጂዱ ማህበረሰብ ምቹ የፀሎትና የመኖሪያ አካባቢ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በበዓላት ወቅትም የዛፎቹ ጥላ ለእንግዶች ማረፊያም ሆነ ለሰላት መስገጃነት ሰፊ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

መስጅዱ የእስልምና ኃይማኖት ከማስፋፋትና ከማጠናከር አንፃር የቁርዓን ንባብና ትርጉም (ተፍሲር)፤ተጅዊድ፤ተውሂድ፤ፊቅህና ሀዲስ ትምህርት በመስጠት እምነቱ ይዘቱን ሳይለቅ ለተከታይ ትውልድ በማስተላለፍ በኩል የጎላ ሚና አለው፡፡ በመስጅዱ ውስጥ ብዛት ያላቸው ተማሪዎች በአዳሪና በተመላላሽ መልኩ ይማራሉ፡፡ መስጅዱ በአጠቃላይ ኃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ልማታዊ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል

የእስልምና ኃይማኖት ትምህርትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የተለያዩ የግብርና ልማት ስራዎች (ከብት ማደለብ ዘመናዊ የንብ ማነብ ስራ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ) በተፈጥሮና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ላይ ችግኝ በማፍላትና በማሰራጨት ለአከባቢው /ሰብና ለሌሎችም ከፍተኛ ጥቅም በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

የቃጥባሬ መስጅድ ክብረ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን በተለይ የብሔራዊ መውሊድ በዓል ተከትሎ የሚከበረው ዓመታዊ ክብረበዓል በርካታ (40 ሺህ በላይ) ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በሚመጡ የእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚዎች ይከበራል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአከባቢውና ዙሪያ ገብ ባሉ ወረዳዎች በሚገኝ ኅብረተሰብ ብቻ የሚከበር የእስነይን(ነብዩ መሀመድ(ሰዐወ) የተወለዱበት ቀን) በዓል በየሳምንቱ ሰኞ ዕለት ይከበራል፡፡

የቃጥባሬ መስጅድን ለመጎብኘት ሲመጡ ሞቅ ደመቅ ያለችውን የዞኑና የቀቤና ወረዳ ርዕሰ ከተማ ወልቂጤንና በመስጅዱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙት የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎች ፣የልማት ስራዎች(አትክልትና ፍራፍሬዎች)፣የጣጤሳ ከብት እርባታ ማዕከል፣የቀቤና ወረዳ ሜዳማ የእርሻ ማሳ እና የዋቤ ወንዝ ተፋሰስ ተከትሎ የሚገኘው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና የተፈጥሮ ደን እየጎበኙ ጉዞዎ በሀሴት የተሞላ ማድረግ ይችላሉ፡፡

 

 

 

We have 338 guests and no members online